ከሰሞኑ በረከት

 

ስደታ ለማርያም

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጅዋ እና ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሰደድ፡-

በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል አብሳሪነት አምላካችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ወደዚህ ዓለም በመምጣት አምላካዊ ትእዛዝን ተላልፎ ካልተፈቀደለት ገበታ የተመገበውን እና በዚህም ምክንያት ከገነት የተሰደደውን አዳምን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ከተወለደበት ከሕፃንነቱ ጀምሮ ታላቅ የሆነ መከራ እና እንግልት ደርሶበታል፤ ሕማምን እና ስደትን ተቀብሏል። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የበኲር ልጅዋን ጌታችንን በወለደች በአርባኛው ቀኗ እንደ ኦሪቱ ሕግ መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም በሔደችበት ጊዜ አስቀድሞ ትንቢት የተነገረለትና በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ የነበረው አረጋዊው ስምዖን ጌታን ታቅፎ "እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።" ሉቃ.፪፡፴፬-፴፭ በማለት እንደተናገረው ቃል ሔሮድስ ሰማያዊውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን የምድራዊ ንጉሥ አድርጎ በማሰብ እና ሥልጣኔን ይወስድብኛል ብሎ በመፍራት እድሜአቸው ሁለት ዓመት እና ከዚያ በታች የሆኑትን ሕፃናት ለማስገደል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ትእዛዙም ተግባራዊ ሆነ።

 

በዚህም ምክንያት አስቀድሞ በነቢያት የተነገረው ትንቢት ፍጻሜን አገኘ። በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ ተጽፎ ነበርና፡- "የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች" ኤር.፴፩፡፲፭። ሔሮድስም ሕፃናትን ማስጨፍጨፍ በጀመረበት ሰዓት የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሔሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ በማለት ሲነግረው ከዚያው ቀን ጀምሮ እመቤታችን ከልጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሽሽቷን ወደ ግብፅ አገር አድርጋለች።

የሔሮድስ አዋጅ ተግባራዊነት እና የእመቤታችን የስደትዋ ክብደት፡-

የእመቤታችንን የግብፅ ስደት እጅግ መሪር ያደረገው በረሐ ለበረሐ በራብና በጥማት መንከራተቷ ብቻ ሳይሆን በታላቅ ፍርሃት እና ድንጋጤ ልጄን ይገድሉብኛል በማለት የነበራት ስጋት ነው። እስራኤል ከግብፅ ምድር ወጥተው ወደ ቃል-ኪዳን ምድር ለመድረስ መንገድ ሲጀምሩ ፈርኦን ፈረስ ሰረገላውን አሰልፎ በብዙ ሠራዊት ይከታተላቸው እንደነበር ሁሉ ሔሮድስም ጭፍሮቹን በመላክ ጌታን ይከታተለው ነበር። በእባብ ላይ አድሮ ከሔዋን ጋር ይነጋገር የነበረው የጥፋት መንፈስ እናንተ በማለት ለአዳም እና ለሔዋን የራራ በመምሰል ከገነት መካከል ከምትገኛዋ ፍሬ መብላት እንደ አምላክ ለመሆን ያስችላል ብሎ በመዋሸት ተሰናክለው እንዲወድቁና ትእዛዝን እንዲተላለፉ በማድረግ ከአምላካቸው አለያይቶ ገነትን ያዘጋባቸውና ከክብራቸው ያጎደላቸውን አዳምን እና ሔዋንን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብራቸው መልሶ ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንዳያሰጣቸው አሁን ደግሞ መልኩን እና አሠራሩን በመቀየር በሔሮድስ ላይ አድሮ በጌታ መወለድ ዓለም እንደሚድን እና የተዘጋው ገነት እንደሚከፈት ስለሚያውቅ ሕፃናት ሁሉ በያሉበት እንዲገደሉ አስደረገ። የዚህ መራራ ፅዋ ዕጣ በልጅዋ ላይ እንዳይደርስ እመቤታችን በከባድ ጭንቀት እና ስጋት ስደትን ለመቅመስ ተገድዳለች። ይኽ ጉዞ ግን ምን ያህል አስቸጋሪ እና ውስብስብ እንደነበር ለመግለፅ ተመጣጣኝ ቃላት አይገኝለትም።

የልጅዋ የወዳጅዋ የኢየሱስ ክርስቶስ እድሜ ሔሮድስ ባወጀው አዋጅ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑና ብዙ ሕፃናትም የተገደሉ በመሆናቸው ኀዘንዋ መሪር እና ክቡድ እንደነበር አባቶቻችን መከራዋን እና ስቃይዋን በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ተረድተው በድርሰቶቻቸው ላይ ጽፈውልናል። በዚህ ስደታቸው ወቅት እመቤታችን ከነልጅዋ እና አረጋዊው ቅዱስ ዮሴፍ እና ሰሎሜ በመንገዳቸው ላይ መጥፎም ጥሩም ሰዎች አጋጥመዋቸዋል። አዝነው ያስጠጓቸው እና የተንከባከቧቸው ሰዎች ነበሩ፤ ደፍረው የሰደቧቸው እና ያባረሯቸው ሰዎች ነበሩ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከደረሰባት መሪር ኀዘን የተነሣ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሁሉ ልጄን ይገድሉብኛል ከማለት ሳታስብ የቀረችበት አንድም ጊዜ አልነበረም። በመንገድ ላይ ሳሉም ዘራፊዎች አጋጥመዋቸው ያላቸውን ቀምተዋቸዋል። ጌታችን፣ አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ አርብ በተሰቀለበት ጊዜ ከግራው እና ከቀኙ የተሰቀሉት ዳክርስ እና ጥጦስ እመቤታችን በስደት በነበረችበት ወቅት የጌታን ልብስ ገፍፈው የወሰዱ ሲሆን ፈያታዊ ዘየማን ተብሎ የሚታወቀው ሰው ከጌታ የዘረፉትን ልብስ መመለስ አለብን በማለት እንዲመለስ አስደርጓል። የሽፍታዎቹ መመላለስ እና ልብሳቸውን መግፈፍ እንዲሁም ልብሳቸውን መመለስ ለእመቤታችን መከራ እና ስጋት ጨምረውባታል እንጂ መጽናናትን አልሰጧትም።

ከሦስት ዓመታት በፊት በቤተልሔም ሳሉ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ ሔሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ ብሎ እንደነገረው ከሦስት ዓመታት በኋላም የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ። ማቴ.፪፡፲፱-፳ በማለት መልእክት አሰምቶታል። በነቢዩ በኢሳይያስ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች። ኢሣ.፯፡ ፲፬ ተብሎ የተነገረው የትንቢት ቃል ፍጻሜ አግኝቶ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ጌታችን እንደተወለደው ሁሉ በነቢዩ በሆሴዕም እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። ሆሴዕ ፲፩፡፩ የተባለው ቃል ፍጻሜን አግኝቶ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ሒድ ያለው መልአክ ሕፃኑን እና እናቱን ይዘህ ተመለስ በማለት ለአረጋዊው ለቅዱስ ዮሴፍ ነግሮታል። የሦስት ዓመት ከስድስት ወር የስደት ዘመን አብቅቶ ከተሰደደችበት ምድር ወጥታ ወደ አገርዋ እና ወደ ምድርዋ ለመመለስ የግብፅን አስቸጋሪ እና አስፈሪ በረሐ አቋርጣ ደብረ ቁስቋም በሚባል ቦታ ከልጅዋ ጋር ሕዳር ፮ ቀን ገብታለች። እመቤታችን ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በግብፅ በረሐ ለመቀመጥዋ እና በስደት ለመውጣትዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ የዮሐንስ ራእይን ይመለከቷል።

የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።...አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። ራእይ. ፲፪፡፩-፮ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስትወልድም፣ ስትሰደድም ሆነ ከስደት ስትመለስ የእግዚአብሔር መልአክ በገሐድ እየተገለጠ በሚነግራት ዜና ነው።

ከመስከረም ፳፮ - ኅዳር ፮ ቀን ድረስ የሚታሰበው ሰቆቃወ ድንግል። (ዘመነ ጽጌ)

ከመስከረም ፳፮ - ኅዳር ፮ ቀን ድረስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን ስደት በማሰብ፣ ራብና ጥሙ እንዴት እንደነበር በመግለጽ፣ በመንገድዋ ላይ ያጋጠማትን ሁኔታ በመዘከር እና በአጠቃላይ ሰቆቃወ ድንግል እንዴት እንደነበር በማስታወስ ባሉት ሳምንታት ሁሉ በማሕሌት ስታነሣት ትገኛለች። በእነዚህ ወራት ባሉት የማሕሌት እና የዝማሬ ጊዜያት አባ ጽጌ ድንግል እና ቅዱስ ያሬድ በደረሷቸው ዜማዎች ሌሊቱን በሙሉ ስደትዋ ሲነገር እና ስትመሰገን ታድራለች። የእመቤታችንን የስደትዋን ነገር በማሰብ ዘመነ ጽጌን በሙሉ በጾም የሚያስቡ ክርስቲያኖች እጅግ ብዙ ናቸው። እንዲህ እንደዛሬው መጓጓዣ እንደ ልብ በማይገኝበት እና መንገድ ባልተሠራበት ዘመን የአገሩ ንዳድና የምድሩ ቃጠሎ እንደ እሳት በሚጋረፍበት የግብፅ ምድር ውስጥ ሦስት ዓመት መቀመጥ ምን ያህል ከባድ ነው? ከካይሮ ከተማ ሁለት ሰዓት ያህል ወጣ ብሎ የሚገኘው ቁስቋም የተባለው ስፍራ እና እመቤታችን ከልጅዋ ጋር ያረፈችበት ቦታ አሁን ድረስ በመጎብኘት ላይ ይገኛል። ቦታው በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን ታንጾበታል፤ እንደ ገዳም ሥርዓትም ንፍሮ ተቀቅሎ ይመገቡበታል፤ ስፍራውም በታላቅ በረከት ተሞልቶ ይስተዋላል። ከላይ በስፋት ለመግለጽ እንደተሞከረው የእመቤታችንን የስደትዋን ነገር ቅዱሳን አባቶች አምልተው እና አስፍተው የመጻፋቸው ጉዳይ ከመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተነሣ ነው። ሱባኤ እየገቡ፣ ጸሎት እያደረጉ እና ፆምን እየፆሙ እመቤታችንን በመማፀን የስደትዋ ዘመን እንዴት እንደነበር በመጠየቅ የነበረውን መከራ እና እንግልት ሁሉ በመጻፍ ታሪክ ዘግበው ያስቀመጡልን አባቶቻችን ባለውለታዎች ናቸው።

ከእመቤታችን ስደት የምንማረው እና የምናገኘው ትምህርት፡-

ስደት እና ጦርነት፣ ማዕበል እና የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ ክስተቶች መቼ እና እንዴት እንደሚፈጸሙ የሚያውቅ ማንም የለም። ትናንት በተድላ እና በደስታ ይኖር የነበረ ሕዝብ ዛሬ በአንድ ቀን ጀምበር ታሪክ ተለውጦበት ደስታው ወደ ኀዘን፣ ሣቁ ወደ ለቅሶ፣ ማግኘቱ ወደ ማጣት፣ ሀብቱ ወደ ድህነት ሊቀየር ይችላል። እንኳንስ ሁሉ ከንቱ ከሆነበት የዓለማችን ምድር እና አኗኗር ቀርቶ ሁሉ እንደ ልብ ከተበረከተበት ከገነት ውስጥ እንኳን ስደት ለመኖሩ መጽሐፍ ይነግረናል። ጠቢቡ ሰሎሞን የዚህን ዓለም ገጽታ በጻፈበት አንቀጹ እንዲህ ይለናል፡- ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። መክ.፫፡፩-፰ ከዚህ መልእክት የምንረዳው ተስፋ መቁረጥ ተገቢ አለመሆኑን ነው። ምክንያቱም በኑሮአችን ውስጥ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ጊዜው ይርዘምም ይጠርም ሊቀሩ የማይችሉ የተፈጥሮ ክስተቶች ናቸው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ስደት የምትሔድበት ጊዜ ነበር፤ ከስደትም የምትመለስበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም ምንም ኃይለኛ ነገር ቢያጋጥመን ጊዜውን ጠብቆ ያልፋል በማለት በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ እንጂ መልስ እንደሌለው ጥያቄ አድርገን በመቁጠር ተስፋ መቁረጥ አያስፈልገንም። ጌታ በወንጌሉ "ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።" ዮሐ. ፲፬፡፲፰ በማለት ዘላለማዊ የሆነ የመጽናናትን ቃል አሰምቶናልና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እኛ የእግዚአብሔር ከሆንን ፈተናችን ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ አለመሆኑን በጠቀሰበት ምእራፉ እንዲህ ይለናል፡- ነገር ግን የኃይሉ ታላቅነት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳይሆን ይህ መዝገብ በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን፤ በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን።፪ቆሮ.፯፡፬-፯ ስለዚህም መገፋት ቢኖር መጨነቅ እንደሌለብን፣ ማመንታት ቢኖር ተስፋ መቁረጥ እንደማይኖርብን፣ መሰደድ ቢኖር መጣል እንደሌለብን፣ መውደቅ ቢኖር መጥፋት እንደማይኖርብን አስተምሮናልና ሁልጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር በወጀብ እና በአውሎ ነፋስ መካከል መንገድ አለው ብሎ በማመን የምድሩን መከራ ሁሉ ልንታገሰው እንጂ ተስፋ ልንቆርጥበት አይገባንም።

ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በረከት እና ረድኤት አምላካችን፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይክፈለን።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር።