የሁለቱንም ቀን ጉባኤ በተመለከት የተዘጋጀውን ሪፖርት፣ ፎቶና ቪዲዮዎች ይህንን ሊንክ በመጫን ይመልከቱ(ተጨማሪ ያንብቡ )
የቅዳሜው መርሐ ግብር ከጠዋቱ 3.30/ 9.30 a.m/ ተጀምሯል፡፡በዚህ ቀን በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ አባላት ቁጥር ጨምሮ ከ፲፬ ክፍለ ግዛቶች/ States/ ከ ፳፭ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ቁጥራቸው ወደ ፪፻ የሚደርስ የሰንበት ት/ቤት አባላት ተገኝተዋል፡፡ በቅዳሜው ጠዋት መርሐ ግበር ላይ ሰፊውን ሰዓት ይዞ የነበረው በ ዲ.ዳንኤል ክብረት ‘’የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የወቅቱ ችግሮች ተግዳሮቶች እና ፈተናዎች’’ በሚል ርዕስ የቀረበው ሰፊና ጥልቅ የሆነው ጥናታዊ ጽሁፍ ሲሆን በቀረበው ጽሁፍ ላይም የቤተክርስቲያንን ችግሮችና ፈተናዎችን በሰፊው አሳይቷል፡፡ በቀረበው ጽሁፍ ላይም የብጹአን አባቶች አስተያየትና የተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦበታል፡፡
በቅዳሜው የከሰዓት በኃላ መርሐ ግብር ሰፊውን ሰአት ከያዙት መርሐ ግብሮች አንዱ የነበረው በቀሲስ ዶ/ር መስፍን ተገኝ “በሰሜን አሜሪካ የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን አህጉረ ስብከትን ለማጠናከር ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችና የሰንበት ት/ቤቶች ድርሻ” በሚል ርዕስ የቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ሲሆን በጽሁፉ ላይም አህጉረ ስብከቶች ያለባቸውን ችግርና የመፍትሔ ሐሳቦችን የጠቆመ ነበር፡፡በየመርሐ ግብሩ መካከል ከተለያዩ ሰ/ት/ቤቶች የመጡ አባላት በተናጥልና በህብረት በመሆን የተለያዩ ያሬዳዊ ዝማሬዎች እና መንፈሳዊ ግጥሞች አቅርበዋል፡፡ ይህ ደግሞ ጉባኤውን አስተማሪና የተለያዩ ሰ/ት/ቤቶች ልምድ የሚለዋወጡበት እና የተሻለ አገልግሎት ለማቅረብ የሚተጉበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዚሁ የቅዳሜው መርሐ ግብር ላይ የአብዛኛው አባላትን ትኩረት የሳበውና የራሱን መንፈሳዊ ህይወት እንዲዳስስ ያደረገው መርሐ ግብር ደግሞ በ፲፪ ዓመቱ ወደ አሜሪካን አገር ከቤተሰብ ጋር የመጣውና የተቀበለውን የማዕረገ ዲቁና ትምህርት ይበልጥ ለማስፋፋት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ለ ፫ ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ ገዳማት ለመንፈሳዊ ትምህርት በሄደው በዲ. ኤፍሬም ስለሺ ህይወት ዙሪያ የተደረገው ቃለ መጠይቅ ነበር ፡፡
እሁድ ጠዋት ጉባኤውን ለመባረክ እና ለመምራት በመጡት ሊቃነ ጳጳሳት ስርዓተ ቅዳሴ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት(በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም እና በደብረ ገነት ኪዳነ ምህረት)ተከናውኗል፡፡ የከሰዓት በኃላውን ሰፊውን ሰዓት ይዞ የነበረው መርሐ ግብር ደግሞ የአንድነት ጉባኤው የአራት አመት ስልታዊ ዕቅድ/strategic plan/ ሲሆን ይህ ስልታዊ ዕቅድ የአንድነት ጉባኤው በቀጣዮቹ አራት ዓመታት እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ ሊያከናውናቸው ይገባል ያላቸውን ነጥቦች አስቀምጧል፡፡ በዚህ ርዕስ ዙሪያም አባላትን በአምስት ምድብ በመከፋፈል ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኃላ የተሰጡት ሃሳቦች በአንድነት ተጠቃለው ለስራ አመራሩ ተሰጥቷል፡፡
የእሁድ ዕለት የማጠቃለያ መርሐ ግብር የነበረው የአንድነት ጉባዔውን የገንዘብ አቅም ለማጠናከር የተደረገው ውይይት ሲሆን በዚህ ውይይት አብዛኛው አባላት ለአንድነት ጉባኤው ያለውን የእኔነት ስሜት ያሳየበት ነበር፡፡በዚሁ መርሐ ግብር ላይም የጉባዔውን የገንዘብ አቅም ለማጠናከር በተደረገው ልዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር አማካይነት ከጉባኤው ተሳታፊዎች እና ጉባኤውን በመገናኛ ብዙሃን ከሚከታተሉ ወንድሞች እና እህቶች አስር ሺህ/፼/ ዶላር እና ለሊቃነ ጳጳሳት ሶስት የአውሮፕላን ቲኬት ወጪ ለማሰባስብ ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ የዘንድሮው ፲፩ኛ ዓመት ጉባኤ የተሳካና የሰ/ት/ቤት አባላቱ የአንድነት ጉባኤውን ለማጠናከር፤ ከአባቶች ጋር አብሮ በመስራት አህገረ ስብከትን ለማጠናከር ተነሳሽነታቸውን ያሳዩበት ነበር፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በገሊላ ቃና በዶኪማስ ቤት ድንግል አዛኝቱ የአምላክ እናት እድምተኛው በዝቶ ወይኑ ሲያልቅባቸው ጥብብ ጭንቅ ሲሉ ማጠፍያው አጥሯቸው ወይኑ በማለቁ ዳር ይደርሳል ያለው ተክዟል ዶኪማስ አለሁልህ በለው ልጄ ወይኑ አለቀ ብለሽ ስትነግሪው ጌታም በመታዘዝ ልዩ ወይን ሰጣቸው ብለሽ እንዳማለድሽ ከእፍረት እንዳዳንሽው ስለእኔም ባዶነት የኔ ጌታ በይው:: (ተጨማሪ ያንብቡ )